Tuesday, February 25, 2014

ኦርቶዶክስ ማለት ምን ማለት ነው፡፡

                                                                                    ከዲ/ን አቤል ኃይሉ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
ዘለዓለም አሜን

 


ኦርቶዶክስ የሚለውን ቃል ኦርቶ/ortho/ ና ዶክሲ/doxy/ ከተባሉት ሁለት የግሪክ ቃላት የተወሰደ ሲሆን ኦርቶ ማለት /ርቱእ/ ቀጥተኛ /direct/ ማለት ሲሆን ዶክስ ማለት ደግሞ እምነት /አስተሳሰብ /ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ እምነት ማለት ነው፡፡
በክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቤ/ክ ኦርቶዶክስ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በ3...
25 ዓ.ም በጉባኤ ኒቂያ ነው፡፡ /synod of Nicene/ ምክንያቱ ደግሞ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ቅድስት ቤ/ክ በክርስቶስ ደም ተመስርታ ምዕመናን በእርሷ ጥላ ውስጥ ማረፍ ከጀመሩ በኋላ ነገሮች ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል አልነበሩም ፡፡ መስራቹን ክርስቶስን ወደ መቃብር ያወረዱት አይሁዶች ክርስትናንም ግብዓት መሬቱን የፈጸሙላት መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ ክርስትናም አብሮ ነበር የተነሳው፡፡ ባረገ በ10ኛው ቀን ኃይል መንፈስ ቅዱስን ከአርያም ልኮላቸው ቅዱስን ሐዋርያቱና ሌሎቹ የክርስቶስ ቤተሰቦች ከእርጅናቸው ታድሰው፣ ከፍርሀታቸው ታክመው፣ ድኑዓን ሆነው፣ የክርስትናን ሠንደቅ ዓላማ ያለምንም መረበሽ በአይሁድ ሰፈሮች ውስጥ እያውለበለቡ መሄድ ጀመሩ፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ዛቻን፣ ማስፈራሪያ፣ ግርፋትና ፣መታሰር ዘወትር ሽልማታቸው ሆነ፡፡ ነገር ግን ይሄ ነገር አጥንትና ደማቸው የሆነውን ክርስቶስን ሊያስተዋቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል እያሉ ምስክርነታቸውን ሰጡ ፡፡ ሥራ 5÷29

አብዝተው በገረፏቸው መጠን የእግዚአብሔር ቃል በዚያው መጠን እየሰፋ መጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም የደቀመዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፡፡ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖቱ የታዘዙ ሆኑ፡፡ የአገልግሎቱም መንኮራኩር ለማፋጠን በመልካም የተመሰከረላቸውን፣ መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን፣ ሰባት ሰዎች ተመርጠው በእጅ መጫን ህብተ ክህናት ከተሰጣቸው በኋላ እስጢፋኖስን ሊቀ ዲያቆናት አድርገው ሾሙት፡፡ እርሱም ጸጋንና ሀይልን ተሞልቶ በህዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር ፡፡ታዲያ ከቀሬናና ከእስክንድርያ ከኪልቅያና ከእስያ የነበሩ የአይሁድ ሰዎች መጥተው ሊከራከሩት ይወዱ ነበር፡፡ነገር ግን ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ ይቃወም ዘንድ አልቻሉም ፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የሰድብና ነገር ሲናገር ስምተነዋል የሚሉ የሀሰት ምስክር አስነሱ፡፡ ወደ ሽንጎም አመጡት፤፤ ያዩት ሰዎችም በንዴትና በእልህ ጥረሳቸውን አፋጩበት፡፡ እርሱ ግን ፊቱን እንደመልአክ በጸዳል ያጥለቀለቀውን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ከጠራራ ፀሐይ ይልቅ የበራውን እውነት እርሱን ለመስማት ግድ ለሌላቸው ጆሮዎች አፈሰሰ፡፡ በዚህ ጊዜ የበፊቱ ሳውል የኋላው ጳውሎስ እስጢፋኖስ በድንጋይ በሚወገርበት ጊዜ የወጋሪዎችን ልብስ ይዞ ቆሞ ይመለከት ነበር ፡፡ ሥራ 6÷1-15 ሥራ 7÷1-60
እዚህ ላይ ሁለት ታሪኮች ይነሳሉ፣ አይሁድ እስጢፋኖስን ሲገድሉ የክርስትናው መንኮራኩርን ፍሬም እንይዛለን፡፡ ፍጥነቱንም እንገታለን ብለው ነበር፡፡ የሆነው ግን ይሄ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በእስጢፋኖስ ምክንያት በቤ/ክ ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፡፡ ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ፣ታዲያ እነዚህ ወደ ተለያዩ ሀገሮች የተበተኑት ክርስቲያኖች በሄዱበትና በደረሱበት ቦታ ሁሉ ክርስትናን ሰበኩ፡፡ ቁጥራቸው በዛ፡፡ ስለዚህ የአይሁድ ሴራ ከሸፋ፡፡

ሌላኛው ታሪክ ደግሞ ሳውል ለሚኖርበት የአይሁድ እምነት ተቆርቁሮ ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለመደምሰስ ከሊቀ ካህናቱ የፈቃድ ደብዳቤ አውጥቶ ወደ ደማስቆ( ሶርያ) ተመመ ፡፡ ወደ ደማስቆ ሲቀርብ ከሰማይ ባንፀባረቀ ታላቅ ብርሃን ተመትቶ ወደ ምድር ወደቀ ፡፡ ‹‹ሳወል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” ሥራ 9÷4 የሚል ድምጽን ሰማ፡፡ ‹‹አንተ ማነህ የማሳድድህ አለው?››፡፡ ክርስቶስም ‹‹አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፡፡ የመውጊያው ብረት ብታቃወም ላንተ ይብስብሃል›› ፡፡ አለው በዚህ ቃል ሳውል ያሳድድው የነበረውን እምነት ወደ ድንኳን ለመመለስ በነገስታትና በእስራኤል ልጆች ፊት የጌታን ስም የሚሸከም ምርጥ ዕቃ ለመሆን ቆርጦ ተነሳ፡፡
ምንም እንኳ አይሁዳውያኑ ክርስትናን ከወለል በታች ለማድረግ ቢሯሯጡም ትናንት ከእነሱ ጋር ይሯሯጥ የነበረው ጳውሎስ የክርስትናን ዕቃ ይዞ ከየትኞቹም አገልጋዮች በላይ መፋጠንን ስራው አደረገው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ንጉስ ‹‹የተወጋነው ከኛው ክንፍ በተወሰዱ ላባዎች ነው’’ እንዳለ በአንድ ወቅት ከእነርሱ ጋር ስለ ኦሪትና ግዝረት ስሌሎችም በክርስቶስ አካልነት ምክንያት ስላለፉት ጥላዎች ቋሚነታቸውን ደግፎ ይከራከር የነበረው ጳውሎስ ዛሬ ግን እውነቱን ተረድቶ ያለፈውን ህይወቱን እየገረመው በሥጋ የአብርሃም ልጆች ሆነው ነገር ግን ከመንግስት ሰማይ በአፍኣ/ በወጭ/ ይጣሉ ዘንድ ስላላቸው ለእስራኤል ዘሥጋ ድህነት አዲሲቱን ህግ ወንጌልን ያውቁ ዘንድ የብርታትን ዝናር ታጥቆ ተነሳ፡፡ ፊትህን ካላየን ማደር አይሆንልንም እያሉ ይናፍቁት የነበሩት ረበናተ አይሁድ /መምህራን አይሁድ/ ቅዱስ ጳውሎስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የሚጠሉት፣ ሊገድሉት የሚፈልጉት ጠላታቸው ሆነ፡፡ እርሱ ግን ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለው›› እያለ በምድረ ፍልስጥኤም የተጀመረችውን ክርስትናን ወደ አህዛብ ሀገር በሚገርም ፍጥነት አደረሰ፡፡ ክርስቲያኖችም ቁጥራቸው እየበዛ ሄደ፡፡

ነገር ግን ቁጥራቸው በበዛው ልክ ፈታኛቸውም እንደ አሸን እየፈሉ ነበር፡፡ በተለይም በአህዛብ ሀገር ጣኦታቱን የማያገለግሉ ካህናት ጣኦታት በጣኦታቱ ስም ከህዝብ የሚያገኙት ገቢ ስለተቋረጠባቸው ክርስትናን ድራሹን ለማጥፋት ተነሱ፡፡ ይህንን በተመለከተ የመጀመሪያውን ትልቁን ስደት ያወጀው ከ54-68 ዓ.ም በሮም የነገሰው ኔሮን ቄሳር ነው፡፡ ይህ ሰው ፍፁም ጨካኝ ነበር፡፡ በሮማ መንበር ላይ በነገሰ በዓመቱ የአባቱን ልጅ አስገደለ፡፡ ቆይቶ ደግሞ እናቱን በመርዝ ገደለ፡፡ በዘመነ መንግስቱ መገባደጃ ላይ ሚስቱን ፣እያስተማረ ያሳደገውን መምህሩን አስገድሏል፡፡ ኔሮን ቄሳር ክርስቲያኖችን ለመፍጀት መነሻ ያደረገው የሮማን ከተማ መቃጠልን ተከትሎ ነው፡፡ ለከተማይቱ መቃጠል ዋናው ምክንያት የሮማ አማልክት በክርስቲያኖቹ ተቆጥተው በከተማይቱ ላይ ወረዳ መቅሰፍት ነው ብለው ካህናት ጣኦታቱ ማስወራት ጀመሩ ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ሥጋቸው እንደሽንኩርት ተቀረደደ ፣ በፈላ ዘይት ተቀቀሉ፡፡ ብዙ ግፍና መከራ ደረሰረባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ . ቅዱስ ጳውሎስ አንገቱን ተሠይፎ በሰማዕትነት ያለፉት፡፡ ይህ እልቂት ከኔሮን ቀጥሎ በተነሱት በዶሚኒያን (81-96 ዓ.ም)፣ትራጃን /98-117ዓ.ም/ ፣ዲዮቅልጥያኖስ /250-305ዓ.ም/ በከፍተኛው ሁኔታ ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖች በካታከምብ/ የምድር ጉድጓድ / እየኖሩ አንድነታቸውን ግን እየጠበቁ ኖረዋል፡፡ ከደረሰባቸው ጭፍጨፋ በተጨማሪ በሲሞን መሠርይ የተጀመረው ምንፍቅና በግኖስቲኮችም ቢቀጥልም ቤተ ክርስቲያን ግን አንድነቷን እየጠበቀች ክርስትና የሚለውን ስም ይዛ ቀጥላ ነበር፡፡
በኔሮን ቄሳር የተጀመረው ክርስቲያኖችን የመጨፍጨፍ አባዜ 312 ዓ.ም ላይ በነገሰው በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ዕረፍት አገኘች፡፡ ቤ/ክ መብቷ ተከበረላት፡፡ ታዲያ ቤ/ክ ከወራሪ ጠላቶች አርፉ የሰላም አየር መተንፈስ በጀመረችበት ወቅት በረጅሙ የቤ/ክ ተጋድሎ ዘመን ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የኖረው ኑፋቄ ትምህርት በአርዮስ አማካኝነት በይፋ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡

በ257 ዓ.ም ወደ ዚህች ምድር የመጣው የሊቢያው ተወላጅ አርዮስ በ3ኛው መ/ክ/ዘመን አካባቢ በተመሠረተው በአንጾኪያ ት/ቤት ሉቅያኖስ ከተባለው መናፍቅ ዘንድ ተምሯል፡፡ከአንጾኪያ ት/ርቱን ጨርሶ ያቀናው ወደ ግብጽ እስክንድርያ ነበር፡፡ በወቅቱም የእስክንድርያ 17ኛው ፓትርያርክ ከነበሩት ከአባ ጴጥሮስ ዲቁና ተቀበሎ ማገልገል ጀመረ፡፡ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው’’ የሚለውን በአንጾኪያ ሉቅያኖስ ጭኖ የላከውን ክህደት በእስክንድርያ ቤ/ክ ለማራገፍ ሲውተረተር ቅዱስ ጴጥሮስ ደርሶበት ትህትናን በተመላበት አነጋገር ‘’ልጄ ሆይ ይህንን ነገር ከእኔ አልሰማኸው፡፡ ከመጽሀፍም አላገኘኸው፡፡ አስበኸው እንደሆነ አትናገረው፡፡ ተናግረኸውም እንደሆነ አትድገመው!!’’ ሲል መከረው፡፡አርዮስ ግን ክህደቱን በልቡ ቆጥሮ ከላይ ግን ለይምሰል የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ የተቀበለ መስሎ ክህደቱን ግን ውስጥ ውስጡን ያሰራጭ ነበር፡፡

አንድ ቀን ሌሊትም ቅዱስ ጴጥሮስ በራእይ ‹‹ ቀሚሱ ለሁለት በተቀደደ ሕጻን አምሳል ክርስቶስ ታየው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ደንግጦ ‹‹አንተ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለህምን›› ሲል ጠየቀው፡፡ ጌታም ‹‹አዎን›› ሲል ይመልስለታል፡፡ ታዲያ ‹‹ልብስህን ማን ቀደደብህ›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› በማለት ይመልስለታል፡፡ ይህንን ራዕይ ካየ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ አኪላስና እለ እስክንድሮስ የተባሉትን ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ያየውን ራእይ ገልጾላቸው አርዮስን ፈጽመው እዳያስጠጉት አስጠነቀቃቸው፡፤ እርሱንም አውግዞ ከቤ/ክ አንድነት ለየው፡፡
ከቅዱስ ጴጥሮስ ዕረፍት በኋላ አኪለስ 18ኛው የእስክንድርያ ቤ/ክ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ ፡፡ በነገራችን ላይ በቤ/ክ ዘመነ ሰማዕታት እየተባለ በሚጠራው ወቅት የዘመነ ሰማዕታት የመጨረሻው ሰማእት እየተባለ የሚጠራ በመሆኑ ተፍጻሜት ሰማእት ቅዱስ ጴጥሮስ እተባለ ይጠራል፡፡አኪላስ ፓትርያርክ ሆኖ ከተሾመ በኋላ አርዮስ ባልጀራነቱን ተገን አድርጎ በመቅረብ አኪለስን የውዳሲ ካንቱ ጨው አላሰው፡፡ አኪለስም በውዳሴ ከንቱ መረብ ተጠልፎ ወድቀ፡፡
የመምህሩን ቃል ጥሶ አርዮስን ከግዘቱ ፈትቶ ወደ ቤ/ክ መለሰው አኪላስም በመንበረ ማርቆስ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል እንኳን አልቆየም ሞተ፡፡ አኪላስም ከሞተ በኋላ በ303 ዓ.ም አለ እስክንድሮስ በመንበር ማርቆስ ላይ ተሾመ ፣የአርዮስ ክህደትም እንደ ሰደድ እሳት እየተዘመተ በመሆኑ አርዮስን አስጠርቶ የክህደት ትምህርቱን እንዲያቆም ነገረው፡፡ አርዮስ በእምቢታው ጸና፡፡ ይባስ ብሎ የግጥም ጸጋውን በመጠቀም ለእንጨት ሰባሪው፣ ለውሃ ቀጅው ፣ለሱቅ ነጋዴው ሁሉ ማደል ጀመረ፣

በዚህም ምክንያት ቤ/ክ በጣም እታወከች ስትመጣ በንጉስ ቆስጠንጢኖስ ትዕዛዝ መሠረት በ325 ዓ.ም በታናሿ እስያ ውስጥ በጥቁር ባህር ወደብ አካባቢ በምትገኝ ኒቂያ በተባለች ከተማ ጉባኤ ተደረገ፡፡ ጉባኤው ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› በማለት አርዮስ ያቀረባቸውን ጥቅሶች መረመረ፡፡ ወልድ በባህርይ ፍጡር ከሆነ በመዳን ምሥጢር ላይ ስለሚያመጣው አደጋ ፣ሌሎችም ሀሳቦች በስፉት ተነስተው ተብራሩ፡፡
በተለይ ወጣቱ ሊቀ ዲያቆናት አትናቴዎስ የጉባኤው ፈርጥ ሆኖ ነበር የዋለው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ መልስ ሲሰጥ በማቴዎስ ወንጌል የተማርነው የጠፋው በግ ምሳሌ የሰው ዘርን የሚመለከት ነው፡፡ ፈላጊውም አካላዊ ቃል የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ ነው፡፡‹‹ቃል ፍጡር›› ከተባለ የጠፈው እርሱ ራሱ ነዋ!! ብሎ አትናቴዎስ ለጉባኤው ሲያሰማ አርቶዶክሳውያኑ በደስታ ተዋጡ፡፡ እራሱ የጠፋ ከሆነ ደግሞ ራሱ ሌላ ፈላጊ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሌሎችም ብዙ ጥያቄዎቹ ፉርሽ ተደረጉበት፡፡ 318 ቱ ሊቃወንትም አንድ ልብ ሆነው አርዮስ አልመለስ ቢል ገዝተው ለዩት፡፡ ሊቃውንቱም ከሀዋርያት አባቶቻችን የቀበልነውን እምነት ሳንበርዝ፣ ሳንከልስ ሳናጣምም ቀጥ እንዳለ እናምናለን ሲሉ ኦርቶዶክሳውያን ተባሉ፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክስ ማለት ከሐዋርያት ቀጥ ብሎ የወረደውን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው የሚለውን ትምህርት ያመነ ማለት ነው፡፡

አንዳንዶች ይህንን ቃል ባለመረዳት ሲተቹ ሲሸረድዱ ይስተዋላሉ፡፤ እኛ ግን ይሄ ስም ዋጋ የተከፈለበት ስም እንደሆነ እናምናለን፡፡ አርዮስና አርዮሳውያን ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ቀሚስን ለመቅደድ ሲነሱ እውነተኞቹ ግን ቀሚሱን ሰፍተው የባህርይ አምላክነቱን አምነው ኦርቶዶክስ የሚለውን ካባ ደረቡ፡፡
በዚህ ስም ክርስቶስ ይከበራል፡፡ በዚህ ቤት የክርስቶስ የባህርይ አምላክነቱ እስከ ሙሉ ክብሩ ይመለክበታል፡፡ ስለዚህ ስም ብለው ብዙዎች በቀስቱ ፈት አለፉ፤ ብዙዎች ወደ ስለት፤ ወደ ጉድጓድ ገቡ ፡፡ ለአንበሶች ተሰጡ፡፡ የማይሆኑትን እየሆኑ ይህንን ስም እዚህ አደረሱ፡፤
አርዮስና አርየሳውያን ግን ለእስልምናና ለጀሆቫ ዊትነስ /የይዋሃ ምስክሮች / መሠረት ሆኑ፡፡
ፅሑፋችንን የምንዘጋው ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ በተናገሩት ቃል ይሆናል፡፡

‹‹ከእነርሱም /እስራኤላውያን/ ክርስቶስ በስጋ መጣ፡፡ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፡፡አሜን›› ሮሜ 9÷5

‹‹የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፡፡ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፡፡እርሱም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘላለም ህይወት ነው፡፡ ልጆች ሆይ ከጣኦት ራሳቸውን ጠብቁ ›› 1ኛዮሐ 5÷20-2

‹‹ተዋህዶ›› የሚለውን ቃል በሚቀጥለው ፅሁፍ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ይቀርባል፡፡

መልካም ሳምንት
ወስብሐት ለእግዚአብሄር

ክርስትና ምን ማለት ነው

                                                                               ከዲ/ን  አቤል ኃይሉ


         ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ምን ማለት እንደሆነ እንወያይ!!!!

በመጀመሪያ ክርስትና የሚለ...
ውን ቃል እንመልከት
ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ተከታይ ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ማለት ሲሆን ምዕመናን/አማኞች/ መጅመሪያ በአንጾኪያ ክርቲያን ተባሉ፡፡ ሥራ11፣26 ክርስትና ማለት ደግሞ ያመኑ ክርስቲያኖች የሚከተሉት እምነት ነው፡፡ መስራቹ ደግሞ በገዛ ደሙ ፈሳሽነት ያጸናት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከተመሰረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠረት አይቻልምና፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‘እንዳለ 1ኛ ቆሮ፣11 ኤ.ፊ 2፣20’
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ የተመሠረተችው ክርስትና የአዳምና ልጆቹን የዘመናት እንቆቅልሽ የፈታች፣ የዓመተ ፍዳ መዝገብን የዘጋች ፣መስቀል የእርግማን መልክት መሆኑ ቀርቶ ከቀስቱ የምናመልጥበት ምክንያቶች ሆኖ የተሰጠባት፣ አባ አባት ብለን የምጮህበት የልጅነት መንፈስ የተቀበልንባት ፣የበዛ ትርፋችን የበረከተ መክሊታችን ሆኖልን ዕረፍት ያገኝባት መንገድ ሆናለች፡፡
እርግጥ ነው ከክርስትና በፊትም በኃላ ወደ ፈጣሪ መድረሻ ናቸው ተብለው የተቀየሱ “መንገዶች“ ነበሩ ፡፡አሁንም ቀያሹ እግዚአብሔር ባይሆንም በንስር ፍጥነት ብዙ መንገዶች በመቀየስ ፣ብዙ መሰረቶች በመመስረት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ክርስትና ከነዚህ ሁሉ መንገዶች ወይም እምነቶች በምንድው የሚለው ሰው ቢኖር ልዩነቱ ክርስትና

1.የመገለጥ እምነት ነው፡፡

ክርስትና የመገለጥ እምነት ነው ሲባል በራዕይ በህልም ወይም በትንቢት ለሆነ ነቢይ ተነግሮት በዚያ ነቢይ አነሳሽነት የተመሰረተ እምነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የእስልምና እምነት ለነቢዩ መሐመድ መልአኩ ጅብሪል ከአላህ በተላከው ቃል መሰረት የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ የአይሁድም እምነት እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በሰጠው ዐሠርቱ ትእዛዛት መሰረት ለሕዝበ እስራኤል የተሰራች እምነት ነው፡፡
ክርስትና የመገለጥ እምነት ነው ሲባል ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ይኸውም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከቅድስት ድንግል በነሳው ሥጋ ሰው ሆኖ ተገልጦ የሰራት እምነት ናት፡፡ ክርስትና በራእይ አልመጣችም፡፡ በሕልም ላይም አልተመሰረተችም፡፡ ነገር ግን ራሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ተገልጦ በቤተ ልሔም ተወልዶ ፣ ወደ ግብጽ ተሰዶ ፣ በናዝሬት አድጎ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ ፣ በኪደተ እግሩ ዓለምን እየቀደሰ ፣ ትምህርቱን በስራው እየገለጠ ፣ሁሉን እያሳየ ክርስትና እንዲህ ናት እያለ ክርስትናን መሰረታት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትና የመገለጥ እምነት መሆኗን ሲመሰክር ‹‹ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለው፡፡ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሰረት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ ፣ ለመላእክት የታየ ፣ በአህዛብ የተሰበከ ፣ በዓለም የታመነ ፣ በክብር ያረገ›› 1ኛ ጢሞ 3÷16
ስለዚህ ክርስትና የማይታየው እግዚአብሔር በሚታይ ሥጋ ፣ የማይዳሰሰው ፈጣሪ በሚዳሰስ ሥጋ ተገልጦ ፣ የባዘኑትን በጎች ወደ በረቱ የመለሰበትን አውነት ይሰብካልና ልዩ ነው፡፡ ይህንን እውነት ከክርስትና ሃይማኖት ውጭ የሚሰብክ የለም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡›› 1ኛ ዮሐ 4÷12 በወንጌሉ ላይም ‹‹ ቃልም እግዚአብሔር ነበር፡፡ . . . ቃልም ሥጋ ነው፡፡›› እንዲል ዮሐ 1-1÷14

2. ልዩ ነው፡፡

ሁለተኛውና ትልቁ ነጥብ ደግሞ ከስነ መለኮት ትምህርት አንጻር ከሌሎች ሃይማኖት ክርስትና ልዩ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- የአይሁድ ፣የእስልምና ፣የአፖስቶሊኮች ፣የጂሆቫ ዊትነሶችን ወ.ዘ.ተ እግዜአብሔር አንድነቱን እንጂ ሦስትነቱ አይቀበሉም ፡፡አንዳንድ እምነቶች ደግሞ ወደ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አማልክት ያሏቸው አሉ ፡፡ ለምሳሌ፡ ጥንታውያን ግሪኮች በታላቁ የግሪክ ተራራ አሊምፐስ /Olympus/ ይኖራሉ ተብለው የሚታመኑ ብዙ አማልክት አሏቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል፡ ጁፒተር /የአማልክት ንጉስ/ ፣ጂኖ /የሰማይ ንግስት/፣ አፖሎ/የፀሐይ ፣የመድኃኒትት፣የሙዚቃ ና የግጥም አምላክ ፣ቬኑስ /የቁንጅና የሣቅ፣ የጋብቻ አምላክ/ ፣ኔፕቱን/የውኃዎች አምላክ /፣ ፕላቶ/የሲኦል አምላክ/ ፣አፍሮዳይት /የፍቅር አምላክ/…ወ.ዘ.ተ እየተባሉ የሚጠሩ አማልክት አሏቸው፡፡
ክርስትና ግን ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት እምነቶች በተለየ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርጋ እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው ብላ ታስተምራለች፡፡ አንድነቱ በመፍጠር ፣በመግዛት /መለኮት/፣በፈቃድ ፣በስልጣን ብሎም በአንድ ልብ በማሰብ ፣በአንድ ቃል በመናገር፣በአንድ እስትንፋስ በመተንፈስ አንድነቱ ይገለጻል ፡፡ ስለዚህ “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው ፡፡” ዘጸ 6÷5 ሲል ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ እየገለጸ መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ በ ሌላም ቦታ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ 10÷30 ፣ “እኔን ያየ አብን አይቷል ፡፡ …እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ “ ዮሐ 14 ÷10-11
“የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፡፡…እርሱ ያከብረኛል ፡፡ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፡፡ስለዚህ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ፡፡ “ ዮሐ16÷14
ይኼን አንድነት ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 8÷5-6 እና በ1ኛ ቆሮ 12÷4 ላይ እንዲህ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡
‹መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፡፡ነገር ግን በሰማያት ሆነ በምድር ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ ለእኛስ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፡፡›› 1ቆሮ 8÷5-6
‹‹መንፈስ ግን አንድነው፡፡›› 1ቆሮ 12፡4
ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲህ አብንም፣ወልድንም፣መንፈስ ቅዱስንም አንድ እያለ በመግለጽ ፍጹም አንድነታቸውን በረቀቀ ምስጢር ገለጸ፡፡ስለዚህ ሶስት አማልክት አንልም:: አንድ አምላክ እንላለን እንጂ፡፡ አንድ አምላክ ስንልም በመፍጠር ፣በአገዛዝ ፣ በስልጣን፣ በአንድ ልብ አስቦ፣ በአንድ ቃል ተናግሮ፣በአንድ እስትንፋስ ተንፍሶ፣ በመኖር ይገለጻል፡፡ ይህን ምስጢር በተለይ በዩሐንስ 16፡14 ላይ በሚገርም ሁኔታ ተገልጻል ፡፡ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን ‹‹ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል›› በማለት መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ቃልነትን ገንዘብ አድርጎ በእርሱ ቃልነት የሚናገር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹ ለአብ ያለው ሁሉ የኔ ነው››በማለቱ ደግሞ ወልድ ከአብ ልብነትን ገንዘብ አድርጎ በአብ ልብነት የሚያስብ መሆኑን ይገልጻል፡፡‹‹ እኔና አብ አንድ ነን›› ዩሐ 10፡30 በማለቱ ደግሞ አንድነታቸውን በሚገባ ገልጾል፡፡
ሦስትነታቸውን ደግሞ በስም፣ በአካልና በግብር ይገለጻል፡፡ ለምሳሌ፡-‹‹ እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው›› ማቴ 24፡19 አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ብሎ ሶስትነታቸውን÷ስም ብሎ አንድነታቸውን ገለጸ፡፡ እዚህ ላይ አስተውል፡፡ ስሞች አላለም፡፡ ስም እንጂ፡፡ የተቀረውን ምስጢር በሌላ ጽሁፍ ላይ ይዳሰሳል፡፡ ይህውም ከምስጢሩ ጥልቅት፣ ስፋትአንጻር ነው፡፡
ስለዚህ ክርስትና ልዩ ነው ሲባል ባለብዙ አማልክት አስተሳሰብ(Polytheism) አይሰብክም፡እንደሌሎችም አንድነው ብቻ ብሎ ሶስትነቱን ገሸሽ አያደርግም:: ነገር ግን አንድነቱን ሶስትነቱ ሳይጠቀልለው፣ አንድነቱ ሶስትነን ሳይከፋፍለው ለዘላለም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ተብለው ይጠራሉ እንጂ፡፡

3. በር ነው

ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መዳኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ የበጎች በር ነኝ፡፡ ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦች እና ወንበዴዎች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በጎቼ አልሰሟቸውም፡፡ በሩ እኔ ነኝ፡፡ በኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፡፡ ይገባልም ይወጣልም፡፡ መሰማሪያ ያገኛል፡፡›› ዩሐ 7፡10 እንዳለ ክርስትና ወደ ፈጣሪ መግቢያ ብቸኛ በር ናት፡፡ ያለዚህ በር የሚገባ ቢኖር መሰማሪያ አያገኝም፡፡ለምሳሌ፡- ራሳቸውን የጽድቅ በር አድርገው የመጡ ነበሩ፡፡ይህንን ነገር የከበረው የህግ መምህር ገማልያል በሐዋ 5፡35 ላይ ‹‹የስራኤል ሰዎች ሆይ ስለነዚህ ሰዎች ተጠንቀቁ::ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ እኔ ታላቅ ሰው ነኝ ብሎ ተነስቶ ነበርና፡፡ 400 የሚያክሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ::እርሱም ጠፋ፤የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፡፡ እንደምናምንም ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘምን የገሊላው ይሁዳ ተነሳ፡፡ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፡፡ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ፡፡›› እንዳለ ራሳቸውን የፈጣሪ እንደራሴ፣መልእክተኛ አድርገው ከእርሱ በፊትም ከእርሱም በኋላ የመጡ አሉ ፡፡እውነቱ ግን በር አለመሆናቸው ነው፡፡ ጌታ ራሱን በመልካም እረኛ ልጆቹን ደግሞ በበጎች መስሎ ባስተማረበት 10ኛ የዩሐንስ ወንጌል ም ዕራፍ ላይ እንደዚህ ሰዎችን መንጋውን ለነጣቂ ተኩላ አሳልፈው በሚሰጡ ሞያተኛ መስሎቸዋል፡፡ በማቴዎስ 7፡13 ‹‹ በጠባው ደጅ ግቡ፡፡ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፡፡ ወደ እሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ወደህይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና፡፡ የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው›› እንዳለ ክርስትና ባለጠጋው ጹም'ደሀውን መጽውት፣አንድም ቀኝህን ለመታህ ግራህን መልስለት፣ አንድ ምዕራፍ እንድትሸኘው ቢጠይቅህ ሁለት ምዕራፍ ሂድለት፣ ጠላትህን ውደድ የሚረግምህን መርቅ፣ ለሚያሳድድህ ጸልይለት የምትል ፍጽምት ትርፍት ህግ ነችና የጠበበች ደጅ ነች፡፡
እናም ክርስትና በር ናትና ወደ ጽዮን ተራራ' ወደ ህያው እግዚአብሔር ከተማ ይገባባታል ፡፡ ክርስትና ደጅ ናትና ወደ በኩራት ማህበር' በደስታም ወደተሰበሰቡበት ወደ አእላፋት መላእክት' ፍጹማንም ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች ይገባባታል፡፡
በክርስትና በርነት መሰማሪያ ይገኛል ፡፡በሩ ደግሞ ክርስቶስ ነው ፡፡በዚህ በር ሲታመን ብቻ ወደ አብ ይመጣል፡፡ በዚህ በር ሲታመን ብቻ ወደ መንፈስ ቅዱስ ይቀረባል፡፡ በዚህ በር አንድነቱ ሶስትነቱ ይመሰጠራል፡፡ ይህን በር ያሳወቀን ጌታ ስሙ ከፍ ከፍ ይበል፡፡ በሩን የጠፋባቸውንም ሆነ የተዘጋባቸውን እግዚአብሔር ያስብልን፡፡
ኦርቶዶክስና ተዋህዶ የሚሉትን ቃላት ሰፊ ምስጢራቸውን በቀጣዩ ጊዜ እናቀርባለን፡፡
መልካም ሳምንት
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መናፍቃን ፕሮቴስታንቶች፤በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ክፍል 2

                                                                                                         ከሣቴብርሃን ገ/ኢየሱስ
እንግዲህ ወደ ጥንተ ነገሩ እንመለስና መናፍቃኑ ለዚህ እኩይ አላማቸው መሳካት የሚጠቀሟቸውን ህቡዕ ስትራቴጂዎች እንመልከት፡፡ ምልመላ፡- የጉድ ሙዳዮቹ ወደ ት/ቤቱ አዲስ የተቀላቀሉ የ11ኛ ክፍል ተማሪዎችን ዋነኛ ኢላማ አድርገው በአዲስ አመት አዲስ ክህደት፤አዲስ ብልጠት ፤ለአዲስ... ‹‹ታርጌት›› ይዘው ብቅ ይላሉ፡፡ ይበልጥ ወደ መጤዎቹ ያተኩሩ እንጂ ነባር 12ኞችን መከታተላቸው ያው አይቀርም፡፡ ለኑፋቄ ጦርነት የሚዘምቱባቸውንም ተማሪዎች የሚመለምሉበት የራሳቸው
 የሆነ መስፈርት አላቸው፡፡ የጠለቀ ነገረ ሀይማኖትም ሆነ የምግባር እውቀት የሌለው፤ለሐይማኖቱ ባይተዋር የሆነሠ፤ከቤተክርስትያን የራቀ የማያስቀድስ የማይፆም፤ የማይፀልይ፤ከአባቶች እግር ስር የራቀ፤በስጋ ፈቃድ የወደቀ፤ከቅዱሳት መፃህፍት ያልተጣበቀ ብቻ በእነሱ አስተሳሰብ ብዙ የማይፈትናቸው ሌበራል ክርስቲያን ብጤ ቀዳሚ ምርጫቸው ነው፡፡
ወጥመዶች፡-
የምልመላውን ስራ በስውር ከጨረሱ በኋላ ወደ ስራው በቀጥታ ይሰማራሉ፡፡ ስራውን አሀዱ ብለው የሚጀምሩት እንደማግኔት የየዋሀኑን ልብ ከየአቅጣጫው ከሳበ በኋላ መፈናፈኛ በማሳጣት አጣብቆ እና አንቆ የሚይዝ ወጥመድ መዘርጋት ነው፡፡ ይህ ‹‹ኦፕሬሽን›› በሁለት ነገር ምክንያት በአብዛኛው ይሰካላቸዋል፡፡ ወጥመዶቹ በመንፈሳውያን እይታ ካልሆነ በስጋዊ እይታ የማይታወቁ ብዙዎች እንደ ቀላል የሚያይዋቸው ሳይታወቁ የማጥቃት ሀይል ያላቸው በመሆኑ የሀይማኖት ብሎናቸው የላላ ዝንጉ ተማሪዎች በቀላሉ ይቀበሉታል፡፡ በተጨማሪ አጥቂው ቡድን የተሟላ አደረጃጀት፤የካበተ ልምድና በቂ ስልጠናን ስለወሰደ በብልጠትና በማታለል ስራ የብዙዎችን ልብ ወደ ወጥመዶቹ ይገፋል፡፡ ነገሩን ቅኔ አደረኩት መሰል ወጥመድ የተባሉትን እስቲ
እንያቸው ፡-
1.የመናፍቃንን መዝሙር መስማት፡-
መዝሙር ስላደረገውና ስላላደረገው ስለሚያደርገውም ነገር እ/ር የሚመሰገንበት ሀሌታ፤መሻታችንን የምንጠይቅበት ጸሎትም ጭምር ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ፈጣሪዋን የምታመሰግንበት የራስዋ ህግና ስርአትአሏት፡፡ ሁሉ በህግና በአግባብ በስርአትም
እንዲሆን ታዘናልና፡፡ (2ቆሮ 14፡10) በዜማ ደረጃ በአንፃረ ያሬድ በተረከብው ጥዑም ሰማያዊ ዜማ ‹‹ ለኢትዮጵያዊያን ምግባቸውን ሰጠሃቸው›› (መዝ.74፡14 ) የሚለው ቃለ ትንቢት ይፈፀም ዘንድ ግዕዝ፤እዝል፤አራራይ የተባሉትን የመላእክት እንጀራዎች እየተመገብን እንኖራለን፡፡ በንዋያት ደረጃ አባቶቻችን ቅዱሳን አበው፤ቅዱሳን ነቢያት፤ካህናት በዘመሩባቸው በቅብዓ ሜሮን ከበረው እግዚአብሔር ንብረት በሆኑ ንዋያትበበገና፤በመሰንቆ፤በፀናፅል፤በመቋሚያ፤በከበሮ በመሳሰሉት ለምስጋና እንተጋለን፡፡ ተመልማዮቹ ሌበራል ክርስትያን ተማሪዎች ይህን የአባቶች ስርአትና ትውፊት በቅጡ አያውቁትም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለመንፈሳዊነት ሳይሆን በዳንስና ዘፈን ለዓለማዊነት ያጋደሉ ናቸው፡፡ ይህን ስስ ብልታቸውን ተመልክተው መናፍቃኑ ወትሮም ያዘመሙ ተማሪዎችን በአንደኛው ወጥመድ እንዲወድቁ ያደርጋሉ፡፡ ይኸውም የራሳቸውን ዘፈናዊ መዝሙር እንዲያደምጡ ማድረግ ነው፡፡ በክፍል ውስጥ፤በግቢ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ፤ካፌ ሲሄዱ ወደጫካ ሲሄዱ፤በቡድን አሳይመንት ሲሰጥ ሰብሰብ ሲሉ ብቻ በአገኙት አጋጣሚ እያንጎራጎሩ የ ‹‹ፕሮሞሽን›› ስራ ይሰራሉ፡፡ ቀስ በቀስ እንጉርጉራቸው መወደድ ዜማቸው ቀልብ መሳብ ይጀምራል፡፡ መቼስ አንድ ክፉ ሰው ባልንጀራውን በመርዝ ሊገድለው ቢፈልግ ተስገብግቦ ጣፍቶት ተሻምቶ ሲበላው አንፈርፍሮ ሚገድለው ተወዳጅ ምግብ ውስጥ እንጂ ገና እንዳየው የሚያቅረው እሬት ውስጥ መርዙን
አይጨምርም፡፡ ሰይጣንም እንደዚሁ ነው በየዘመናቱ የሚያስነሳቸውን መናፍቃን ተጠቅሞ የክህደት ዘሩን ለመዝራት ሰዎች
በሚወዱትና በሚደሰቱበት ግን ከንቱ በሆነ ነገር ገብቶ ማሳት ልማዱ ነው፡፡ ‹‹ወልድ ፍጡር በመለኮቱ›› ያለ የመናፍቃን አለቃ አርዮስ ይህን ኑፋቄውን ሲያስፋፋ የነበረው እንዲሁ በደረቁ አልነበረም፡፡ በነበረው የግጥም የመፃፍ ችሎታ ተጠቅሞ የሀሰት ትምህርቱን በየስንኞቹ እየሰገሰገ በዘመኑ ግጥም ወዳድ ለነበረው ማህበረሰብ በተነው፡፡ በቀላሉ
ተቀባይነትንም አግኝቶ በግጥም ቀጭን መንገድነት ሾልኮ በምእመናኑ ልብ ላይ ከነህፀፁ ጉብ አለ፡፡
ዳግመኛ ‹‹ ድንግል ምርያም የወለደችው ሰው ነው ›› ያለው ከአርዮስ የማይተናነሰው የፓትርያርክ መናፍቅ ንስጥሮስ ንግግር አሳማሪና ድምፀ መልካም እንደነበር ይነገርለታል፡፡ ብዙዎች አንደበተ ርቱዕነቱን በማድነቅ አውቀውም ሳያቁትም ተከትለውታል፡፡
በስነ-ፅሑፍና በአንደበተ ርዕቱዕነት ማዳበሪያ ተጠቅሎ ያለን ክህደት ተጭነው ሲነዱ የነበሩ የዳቢሎስ አህዮች አርዮስና ንስጥሮስ ቢሞቱም ነጅው ከነጭነቱ በየዘመን ስለይቀያየር ማዳበርያ ብቻ ቀይሮ ለዘመነኞቹ ተተኪ አህዮች መናፍቃን አስጠግርሯቸዋል፡፡ በዚህ ዘመን የዘፈን ምርኮኛ ያልሆነ ወጣት ብናገኝ እድለኞች ነን፡፡ ስለዚህ አጅሬ ይህችን አጋጣሚ ተጠቅሞ የዘፈን ምት፤የዘፈን ቃና፤ዘፈን ቀለምናሽታያላቸው በስም ግን መዝሙር የተባሉ መናፍቃን መዝሙሮችን ማምረት ማስመረት ጀመረ፡፡ ወጣቱ መንፈሳዊ
ተብለው የሚሰጡት ስመ-መዝሙሮች ዓለምን ካሳበዱ ዘፈን ስልቶች ከነ HIPHOP,JAZZ,REGEE,RAP… ጋር
ተስማማለትና ወደደው፡፡ ነገሩ መላ ያጣ ከመሆኑም የተነሳ ገና በኢትዮጵያ ድምፃውያን ያልተሰራበት ረቀቀ የባህር ማዶ የዜማ ስልት ቀድሞ በፕሮቴስታንት ዝማሬ ላይ እናገኘዋለን፡፡ እንደው ዛሬ በስንቶቻችን ሞባይልና ላፕቶፕ ላይ የመናፍቃን መዝሙር ይገኛል ?
አላስተዋልነውም እንጂ ብዙዎቻችን ወደ ወጥመዱ እየተጠጋን ነው፡፡ ባለፍን ባገደምን ቁጥር አለፍ ስንል ለምንሰማቸው እልፍ መዝሙሮች አንገት ጭንቅላት ነቅነቅ፤መሰጥ፤ሰረቅ፤መጠቅ የምንል ወሰድ መለሶች ሆነናል እኮ ! ከወጥመድ አንድ ያልተነካካን ስንቶቻችን እንሆን ?
ስለሆነም በፍፁም የእነሱን መዝሙር እንዳንሰማ አደራ እላችኋለው፡፡ የእኛም የእነሱም አንድ ነው ካላችሁ ፍፁም ተሳስታችኋል፡፡ እነሱ ከሐዲያን ናቸው የከሀዲ መዝሙር ደግሞ አናደምጥም፡፡
ድንግል ማርያምን የቀደሰ ያወደሰ መዝሙር በሰማንበት ጆሮ እሷን የካዱ የሙታንን መዝሙር ከምናደምጥበት ቢደፈን ይሻላል፡፡
ስለሃዋርያት፤ፃድቃን፤ሰማ ዕታት፤መላዕክት፤ሊቃውንት ውዳሴና
ክብር የሚናገር መዝሙር በአንቆረቆርንበት ጆሮ እንዚህን ፈርጦች በካዱ ምልጃው ፀሎታቸው አይጠቅመንም ባሉ መናፍቃን አንደበት ተቀለፀ መዝሙር መስማት መናፍቅ
ከመሆን የማይተናነስ ሸፍጥ ነው !!
አስቡበት ይቀጥላል . . . . . . . .

መናፍቃን-ፕሮቴስታንቶች በኦርዶክሳውያን ተማሪዎች ክፍል1


 ከ ከሳቴብርሃን ገብረኢየሱስ

መናፍቃን በጌታ አነጋገር ፀራዊ(ክፉ ጠላት) በጌታ ደቀ መዛሙርት በሐዋርያት አነጋገር ቢፅ ሐሳውያን (ሀሰተኛ ባልንጀሮች) በሊቃውንት አነጋገር መናፍቃን ይባላሉ፡፡ ሊቃውንተ ቤ/ክ ለነዚ ከሐድያንይባላሉ ፡፡ሊቃውንተ ቤ/ክ ‹‹መናፍቅ›› የሚለውን ስም ሲሰጡ እንዲሁ በደፈናው አይደለም፡፡ ከነገረ ሃይማኖትም ሆነ ከምግባር ትምህርት ውስጥ ልቦናቸው የወደደውንና ከስጋ ፈቃዳቸው ጋር የሚዛመደውን በእነሱ መንገድ የሚሄደውን ብቻ ነጥለው የሚያምኑ ክፍሎ አማኞች ስለሆኑ ነው እንጂ፡፡ መናፍቅ ‹‹መ...ንፈቅ›› ኪሚለው ቃል የተገኘ ትርጉሙም-ክፋይ፤ እኩሌታ፤ አጋማሽ ማለት ነውና፡፡ በተለምዶ የፕሮቴስታንቱ አለም በዚህ ስያሜ ይጠራ እንጂ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ አምነት ውጭ ያሉ ብዙዎቹ ሃይማኖቶች የዚህ ስም ድርሻ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሙስሊሞች ከአረማዊነታቸው ባሻገር መናፍቃንም ናቸው፡፡ እንዴት ቢሉ ከሚስጥረ ስላሴ የእግዚአብሄርን አንድነት ብቻ ነጥለው ተቀብለው ሶስትነቱን አያምኑም፤ አብ የባህርይ አምላክ እንደሆነ ሁሉ ቅድመ አለም ያለ እናት የወለደው የባህርይ ልጁ ወልድም አምላክ እንደሆነ አይቀበሉም፤‹‹ለሰማይ ደጅ ለአላህ ልጅ የለውም፡፡›› ብለው ያምናሉ እግዚአብሄር አዳምና ሄዋንን (አደም ና ሐዋን) አምላክነትን ፈልገው ባደረጉት አመፅ እንደረገማቸውና ከቀደመው ክብቸው እንደተዋረዱ ያምኑና ከ5500 ዘመን በኃላ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ለአዳም የሰጠውን የተስፋ ቃል፤ ኋላም ቃሉን ሳይረሳ ጊዜው ሲደርስ ወደዚህ አለም መጥቶ ተሰቅሎ እንዳዳነው የሚገልጸውን ነገረ ስጋዌውን ይክዳሉ፡፡ ስለዚህ ከፍሎ አማኞች (መናፍቃን) ናቸው፡፡ ካቶሊኮችም እንዲሁ ናቸው ኢየሱስ ክርስቶሰ ሥጋ ከመለኮት መለኮት ከሥጋ ተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ዳሩ ግን ከኹለት አካል አንድ አካል ከኹለት ባህርይ አንድ ባህርይ መሆኑን ሽምጥጥ አድርገው ሲክዱ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ ከፍሎ አማኞች ናቸው፡፡ የዚህን ፅሑፍ ርዕስ ‹‹መናፍቃን-ፕሮቴስታንቶች…›› ያልኩበት ምክንያት ሌሎችም መናፍቃን እንዳሉ ለማጠየቅ ነው፡፡ የፅሑፉ ዋነኛ አላማ በተለይ በት/ቤ/ት አካባቢ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ከርትዕት- ሃይማኖታቸው አስኮብልለው የክህደት ደቀ-መዝሙር ሊያደርጋቸው ላይ ታች የሚራወጡ የመናፍቃን ፕሮቴስታንቶችን ክፉ ተግባር እንቃወም ዘንድ ማስቻል ነው፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 1000 ዓመት አስቀድሞ በሐልዎተ እግዚአብሔር የነበረውን ኋላም በዘመነ-ሐዲስ ከእስራኤል ቀጥሎ ክርስትናን በመቀበል መፅሐፍ ቅዱስን በራሱ ቋንቋ ተርጉሞ ለ2000 ዓመታት ያህል ወንጌልን ሲማርና ሲሰብክ እግዚአብሔርን ሲያመልክና ሲያስመልክ የኖረውን ፍጹም እምነት ያለው ክርስቲያን ደርሶ ወንጌል እንስበክባላችሁ ጌታን አልተቀበላችሁም ማለት‹‹ ለቀባሪው አረዱት›› እንደማለት ነው፡፡ በቤ/ክ ከጌታ ስም ይልቅ የቅዱሳን ስም ገኖ የሚጠራ ቤ/ክ በወንጌል ሳይሆን በባህል የምትመራ የሚመስላቸው የዋሃን ጥቂቶች አይደሉም፡ ቤ/ክ በገድሉ፤ በድርሳኑ ፤በመልካ መልኩ፤ በድጓው፤ በመፅሐፍቶቿ፤ በቅዳሴዋ፤ በማኅሌቷ ፤በሰዓታቷ በሁሉ ነገሯ ክርስቶስን ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው ውዳሴ ማሪያም 63 በመቶ የሚናገረው ስለ ክርስቶስ መሆኑን ስንቶቻችን አናውቃለን? ትልቅ ነገር የተናገሩ ይመስል ‹‹ኢየሱስ ጌታ ነው! ››ብለው ጆሮአችን እስኪበጠስ ድረስ እንደ ብራቅ የሚጮሁብን ፕሮቴስታንቶች ቤ/ክ ክርስቶስን ‹‹የጌቶች ጌታ፤ የነገስታት ንጉስ፤ የአማልክት አምላክ›› ብላ ባሏት ሃብቶች ሁሉ እንደምታወደሰው ያውቁት ይሆን? ውሻ በጮኽ እቃ በወደቀ ቁጥር እየጠሩ የሚያንገላቱትን ኢየሱስ የሚውለን ስም በስምንተኛው ቀን ያወጣችለትን ድንግል ማርያምን ብናከብር እርሱንና ስሙን አላከበርንም ትላላችሁ? ብዙ ምሳሌ መደርደር ይቻል ነበር፡፡ነገር ግን የፌስ-ቡክ ፅሑፍና የግዢ እንጀራ ለቅምሻ እንጂ ለጥጋብ ስለማይሆን በዚሁ ልግታው፡፡
እውነታውና ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ‹‹ወንጌል እንሰብካለን ፤ጌታን ተቀበሉ›› በሚል ጭንብል ክህደታቸውን ሸፍነው ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎችን ከእውነት መስመር ለማስወጣት የሚማስኑ በተለይ በኛው ግቢ አሳላ ፕሪፓራቶሪ ት/ቤ/ት የሚገኙ ፕሮቴስታንቶች ችንደ አሸን በዝተው አሉ፡፡ አላማቸው ኑፋቄን ዘርቶ ማብቅል፤ኦርቶዶክስን ማዳከም፤ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የደጋፊ ቁጥር ማብዛት ስለ ሆነ ነው እንጂ እንደ ሐዋርያትና አርድዕት የወንጌል ማዳረስ ተልእኮ ቢኖራቸው ኖሮ አረማዊያን ሙስሊሞችን በሰበኩ ነበር ፡፡ በአንድ ወቅት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ወንጌል እንሰብካለን በሚል ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት ሚሲዮኖች የሰጡት ምላሽ ለዛሬዎቹ በሽተኞች ጥሩ መድኃኒት ነው፡፡ አጼ ዩሐንስ ለሚሲዎኖቹ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፡፡ ‹‹እናንተ ወንጌል ለመስበክ የአህዛብን ሃገራት እነ ሊቢያን ፤እነ ቻድን ፤እነ ሱዳንን አቋርጣችሁ የክስቲያን ደሴት ኢትዮጲያ መጣችሁ፡፡ ቀልደኞች! በእውነት እናንተ ሰባኪያነ ወንጌል ብትሆኑ ኖሮ ሳውዲ አረቢያ ሄዳችሁ በሰበካችሁ ነበር››
ይቀጥላle

ከፎቶ ማህደራችን